Kinijitswiss.org contact us
Kinijitswiss.org Kinijitswiss.org Kinijitswiss.org
 


 
main content

በችሎታዎ ፣ በልምድዎ ፣ በተስጥኦዎ የዲሞክራሲ ትግሉን እንዲያግዙ ቅንጅት ጥሪውን ያቀርባል::

የዲሞክራሲ ትግሉን በምን መልክ ማገዝ እችላለሁ?

ግንቦቱ ምርጫ ሰፊ የህዝብ ይሁንታ ያገኘው ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ መሪዎች ላይ የፈጠራና የሃሰት ክስ ተመስርቶባቸው ወህኒ ከተወረወሩ ከአንድ አመት በላይ ተቆጥሯል:: በግንቦት ዘጠና ሰባቱ ምርጫ ቅንጅትን የመረጠውን ሕዝብ የብሄር ፣ የቋንቋ ፣ የፆታ ፣የእድሜ፣ የትምህርት፣ የሃይማኖት ወዘተ ስብጥር ጠጋ ብሎ ላጤነው የቅንጅትን የማሸነፍ ምስጢር ለመረዳት በጣም ከባድ አይሆንበትም::

የቅንጅት የማሸነፍ ምስጢሩ የሕዝብን ድምጽ ማድመጡ ነው:: የቅንጅት የማሸነፍ ምስጢሩ የሕዝብን መብት ማክበሩና የህዝብን ፍላጎት ለማሟላት መሻቱ ነው::

በተቃራኒው አምባገነኖች የመሸነፋቸውና የውድቀታቸው ሁሉ መንስኤ ለሕዝብ እሪታ ጆሮ መንፈጋቸውና የሕዝብን መብት በመደፍጠጥ ጊዜን ለመግዛት መውተርተራቸው ነው::

ሕዝብ ይበጀኛል፣ ያዋጣኛል ፣ ይመራኛል፣ ያስተዳድረኛል; ብሎ የመረጠውን አካል ፣ ማዋከብ ፣ ማሰር፣ ማሳደድ የሕዝብን እሪታ ያባብሳል:: የህዝብን የዲሞክራሲ ጥማት ይብሱኑ ያፋፍማል እንጂ ፈፅሞ አያጠፋውም::

ብልጭ ብሎ የነበረው የዲሞክራሲ ጭላንጭል መልሶ እንዲዳፈን በውስጥም በውጭም መጠነ ሰፊ አፈና እየተካሄደበት ቢሆንም ህዝቡ እምቢኝ ለነጻነቴ - እምቢኝ ለመብቴ ብሎ ሰላማዊ ትግሉን ከማቀጣጠል ከቶ አልቦዘነም:: ግንቦት 7 1997 ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ የለኮሰውን የነፃነትና የዲሞክራሲ ችቦ በየስፍራው እንዲንቦገቦግ ለማድረግና ትግሉን ዳር ለማድረስ እርስዎም ድርሻ እንዳለዎት አይዘንጉ:: ድርሻዎን አሳንሰውም አይመልከቱ::

ይህ አምድ በትግሉ ሜዳ ላይ ያለን የዲሞክራሲ ሃይሎች እርስ በርስ የምንደጋገፍበትን ፣ አንዳችን ጋ ያጠረውን ፣ ሌላችን ጋ ተርፎ የተቀመጠውን ሪሶርስ ( ሃሳብን ፣ ፈጠራን ማቴርያልን ጨምሮ ) ትግሉን በሚያግዝ መልክ ለመለዋወጥ እንዲያገለግል ታስቦ የተዘጋጀ መድረክ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል::

ምንአይነት ተሰጥዖ ወይም ልዩ ችሎታ አለዎት?

በችሎታዎ ፣ በልምድዎ ፣ በተስጥኦዎ የዲሞክራሲ ትግሉን እንዲያግዙ ቅንጅት ጥሪውን ያቀርባል::

  • ገጣሚ ነዎት? ሊቀለበስ የተሞከረውን የኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ጉዞ አስመልክቶ ስንኝ ይቋጥሩ::

  • ሰአሊ ነዎት? በሃገር ቤት የሚፈፅመውን የስባዊ መብት ረገጣ ፣ ስደት ፣ ግርፋት ፣እንግልት የሚያንፀባርቅ የስእል ኤግዚቪሽን ለማዘጋጀት ምን ያስፈልግዎታል? ቦታ? ማቴርያል? ያስፍሩልን:: መልእክትዎን ያነበበ በአቅራቢያዎ ያለ የእርስዎ እጥረት ለሱ ሙላት የሆነው በቀላሉ ሊረዳዎ እንደሚችል አስበው ያውቃሉ?

  • የተለያዩ ቋንቋዎችን የመናገር ችሎታ ካለዎት ለትግሉ በጣም ያስፈልጉታል:: ወደተለያዩ አለም አቀፍ ቋንቋዎች መተርጎም ያለባቸው በርካታ የትርጉም ስራዎች አሉ:: ስብሰባዎች ላይ ወደአካባቢው ቋንቋ በንግግርና በፅሁፍ በመተርጎም ትግሉን ሊያግዙ ይችላሉና ችላ አይበሉ፣ ስራውንም እንደቀላል አይመልከቱት::

  • ካርቱኒስት ነዎት? ካርቱን የመሳል ችሎታ የሌላቸው በርካታ ተቆርቋሪ ወገኖች ብሶታቸውን፣ ስጋታቸውን፣ ፍርሃታቸውን፣ ተስፋቸውን፣ ምኞታቸውን በካርቱን ስእል የሚገልፅላቸው አጥተው በእጅጉ ይፈልጉዎታል::

በምን የስራ መስክ ተሰማርተው ነው ያሉት:: መምህር ነዎት? የሙዚቃ አዋቂ ነዎት? ላገኙት ሰው ሁሉ የሃገራችንን ሁኔታ የማስረዳት ሃላፊነት አለብዎት:: ከወዳጆችዎ ከጓደኞችዎ ከቤተሰብዎ ጋር በሃገራችን ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ጊዜ ሰጥተው ይወያዩ:: መሪዎቻችንን ለማስፈታት በሚካሄዱ ዝግጅቶች ስብሰባዎች ፣ ሰላማዊ ሰልፎች ወዘተ ይሳተፉ::

ሰላማዊ ትግሉ ባለ ብዙ ዘርፍ በመሆኑ የእርስዎ ትንሽ ጥረት ከፍ ያለ ውጤት እንደምታመጣ ይገምቱና ዛሬውኑ ይንቀሳቀሱ:: የቅንጅት ትግል የሕዝብ ትግል ነውና !

ወደ ሚቀጥለው ገጽ ለመሄድ እዚህ ላይ ይጫኑ

 


 
`

@2007 - KINIJIT Support Organization In Switzerland Web Design By SaNet