Kinijitswiss.org contact us
Kinijitswiss.org Kinijitswiss.org Kinijitswiss.org
 


 
main content

ግልፅ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚ/ር መለስ ዜናዊ

ይህችን የኔን አጭር ፅሁፍ ምን አይነት ጊዜ ተርፎዎት ሊያነቡ እንደሚችሉ አላውቅም:: ምክንያቱም እርስዎ በአሁኑ ሰአት ባሰሯቸው በእነዚህ የኢትዮጵያ ብርቅ ዜጎች፣ የነፃነት ጎህ ቀዳጆች እና የቁርጥ ቀን ልጆች በሆኑት የቅንጅት መሪዎች ላይ ለማስፈረድ ነገር እየተበተቡ እንደሆነ በግልፅ የሚታወቅ በመሆኑ ነው::

ይህ ሁሉ መዳከር ደግሞ እርስዎም ሆኑ አጋሮችዎ እውነተኛው ፍርድ በፈጣሪ የሚሰጥ እንጂ የሰው ፍርድ ከንቱ መሆኑን ካለመረዳታችሁ ሳቢያ የሚመነጭ መሰረታዊ ችግር ነው:: (ዳሩ በየትኛው ሐይማኖታችሁ!)

እርስዎ በአሁኑ ሰአት በጣም ሰፊ በሆኑ አራት መስቀለኛ መንገዶች መሓል ላይ የመኪናዎችን አካሄድ ለመምራት የቆሙ ትራፊክ ተመስለው ይታዩኛል:: እናም እነዚህን መኪናዎች በአግባቡ መምራትና ማስተናገድ ባይችሉ፣ ወይም የርስዎ ወዳጆች የያዙዋቸው መኪኖች ወደበዙበት መንገድ ብቻ በማየት ቅድሚያ እየሰጡ የትራፊክ መጨናነቅ ቢፈጥሩ (እየተፈጠረ እንዳለው ) ሁለት ዋነኛ ነገሮች አይቀሬ ናቸው::

1= ሁሉም ሊደርስበት ወዳለው ግብ ለመሮጥ የራሱን መንገድ እየመረጠ ጉዞውን ሲቀጥል እርስዎ በፍፁም መምራት የማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ ይሆኑና መሃል ላይ እንደግዑዝ ሐውልት ቆመው ይቀራሉ:: እርስዎ ሊያስቀድሟቸው ያሰቧቸው የወዳጆችዎ መኪኖችም የርስዎን ዝም ብሎ መቆም ሲያዩ ሌሎች በመረጧቸው አማራጭ መንገዶች ቀስ እያሉ በመግባት አዲስ ጉዞ ይቀጥላሉ:: (በግልፅ እየታየ እንዳለው)

2= ሌላውና አደገኛው:- የተፈጠረው የትራፊክ መጨናነቅ በሚያስከትለው አደጋ የመጀመሪያ ተጠቂ እርስዎ መሐል ላይ የተገተሩት ትራፊክ ተብዬ ነዎት:: አቶ በረከት እና አቶ አዲሱ ለገሰ የሚያሽከረክሯቸው መኪኖች እንኳን ሳይቀሩ በመጨረሻ ሰአት ከትርምሱ ለመውጣት የራሳቸውን መንገድ ይጠቀማሉ:: እርስዎን ጭኖ እንኳን ለመሄድ የሚያቆሙበት ቦታ አይኖራቸውም ወይም አይፈልጉም «ሀ ራስን ማዳን» ይሆንባቸውና::

ጠቅላይ ሚ/ር ሆይ እስከአሁን የሚቻልዎትን ሁሉ አድርገዋል እያደረጉም ነው:: በዚህም የኢትዮጵያን ሕዝብ ዝም ያሰኙ መስሎዎት ይሆናል:: መቼም ግራ መጋባቱ ሕሊናዎትን ደፍኖት እንጂ ብዙ ታሪክ ያውቃሉ:: ከዛሬ መቶ አመት በፊት በታሪክ ልውሰድዎትና ባልሳሳት ዓፄ ምንሊክ ይመስሉኛልሕዝቡ ግብር ጨምሮ እንዲከፍል ትዕዛዝ ቢያስተላልፉ ሕዝቡም በንዴት ጮኸ፣ ይህንንም ባለሟሎቻቸው ወጥተው የሕዝቡን ቁጣ ቢነግሯቸው እሳቸውም «እንግዲያው አሁንም ጨምሩበት ያርፋል::» ብለው ትዕዛዝ ሰጡ፣ አሁንም ሕዝብ ለሁለተኛ ጊዜ ቁጣውን ይበልጥ አሰማ:: ይሄም መልዕክት በድጋሚ ቢደርሳቸው አሁንም በትዕቢት «ለሶስተኛ ጊዜ ጨምሩበት በደንብ ይጩህ » ቢሉ ሕዝቡ ግን ለሶስተኛው ጭማሪ ቁጣውን ትቶ በልቡ እየመከረ ፀጥ አለ:: ይበልጥ ጩኸት የጠበቁት ዓፄ የፀጥታው መልስ ሲነገራቸው « አይ አሁን ነው መፍራት!» ብለው ማሻሻያዎችን ለመውስድ ተገደዋል::

በዚያን ዘመን እንኳ እንዲህ ዓይነት ማስተዋል ታይቷል: እርስዎ ግን ከ 100 አመት በኋላ ዓለም ሁሉ እየሰለጠነ ባለበት ሰአት ማስተዋል ተሳነዎት::እኔ እንኳ በአቅራቢያዬ በማውቀውና በምከታተለው ሁኔታ ልንገርዎት የኢትዮጵያ ሕዝብ አልተኛም- በፍፁም::

ክቡርነትዎ « ለቀባሪው አረዱት» ቢሆንብኝም ጥቂት ነገሮችን ልጨምርና ፅሁፌን ላብቃ:: በአለማችን ላይ የተከሰቱትን የብዙ አምባገነኖችን ታሪክ እንተውና በጣም ጥቂት የቅርብ ጊዜ ትዝታዎችን እንይ::

እውነት እንነጋገር ከተባለ ኮለኔል መንግስቱ በመጨረሻዋ ሰአት ላይ እንኳ በሃገር ሽማግሌዎች ለድርድር እንዲቀርቡ ቢጠየቁ «ይህ የባልና የሚስት የፀብ ጉዳይ አይደለም» ብለው መናገር የቻሉ መስሏቸው ተሳለቁ፣ በኋላም ውርደትን ተቀበሉ:: የላይቤርያው ቻርልስ ቴይለር እንደዚያ ተዋርደው እንደመንደር ውስጥ ሌባ እጃቸውን የኋሊት ታስረው ወደ እስር ቤት ሲወረወሩ ምን እንደተሰማዎት ባላውቅም መቼም አንካካድም አሳምረው አይተዋል::

በርግጥ የሳዳም ሁሴንን ጉዳይ እንዳላየ ቢሆኑ ይሻልዎታል:: እርስዎም እዚያ ደረጃ ላይ ለመድረስ ፉክክር ላይ ካልሆኑ በቀር::

እንግዲህ እነዚህ ሁሉም ነገር ተሟልቶላቸው የነበሩ መሪዎች ይህ ነገር ከኋላቸው እንደሚመጣ ቢያውቁ ኖሮ ያን ሁሉ ደባ አይፈፅሙም ነበር:: በርግጥ በኋላ የሚሆነውን ማንም አያውቅም ግን አካሄድን አይቶ መገመት ይቻላል:: ሰው ደግሞ ካለፉ ስህተቶችና ገጠመኞች እየተማረ ይሄዳል ይህን ካላደረገ ግን መጀመሪያውኑ ስሙ እንጂ በባህሪው ሰው መሆኑ ጥያቄ ውስጥ ይገባል::

እናም ጠቅላይ ሚ/ር እርስዎ አሁን ያኔ እንዳፌዙባት 11ኛው ሰአት ላይ ብቻ ሳይሆኑ የመጨረሻዎቹ ሴኮንዶች ላይ ይገኛሉ፣ እያንዳንዷም ሴኮንድ ነገሮችን ይበልጥ የሚያወሳስቡበት ሳይሆን ለመፍታት ጥረት የሚያደርጉበት ወሳኝ ሰአት ነውና ልብ ሊሉ ይገባል::

ፈጣሪ ዓምላክ መሃሪ ነውና የሚያስተውል ልቦና ይስጥዎት::
ተሻለ ወ/ገብርኤል ( አርጋው - ስዊዘርላንድ)

 


 
`

@2007 - KINIJIT Support Organization In Switzerland Web Design By SaNet