Kinijitswiss.org contact us
Kinijitswiss.org Kinijitswiss.org Kinijitswiss.org
 


 
main content

ማነዉ የሚደሰት?

ማነዉ የሚደሰት ማነዉ የሚጨፍር ?
ሚሊኒየም ብሎ ከወያኔ ጋር።

ጨለማ ለዋጠዉ ላጣ ብርሃኑን
ምድሩን ለተቀማ የያቆብ የኩሽን።
ኃይሉን ላስረከበ ላሟጠጠ ትዕግስት
መሪ ለሌለዉ መስፍን ታግቶበት።
ይሄ ሚሊኒየም ምንድን ነዉ ተስፋችን
ከምንዳክርበት ከማጡ መዉጪያችን።

ማነዉ የሚደሰት ማነዉ የሚጨፍር
ሚሊኒየም ብሎ ከወያኔ ጋር።

ታላቅ ሚሊኒየም ድንቅ የታየበት
ሰርክአለም ቃሊቲ የወለደችበት።
አባቱ እስክንድር በግፍ የሚማቅቅ
ይህ ነዉ ሚሊኒየም አለምን ሚያስደንቅ።
የወጣት የህፃን የሽብሬዎች ደም
ገና መች ደረቀ ልንል ሚሊኒየም።
ማነዉ የሚደሰት ማነዉ የሚጨፍር
ሚሊኒየም ብሎ ከወያኔ ጋር።
ደበበ ግዛቸዉ ብርቱካን ሚደቅሳ
ምን በበደሉ ነዉ የሚያዩት አበሳ።
መቼ ኢዩኤል ብቻ ታጎረ ቃሊቲ
እዉቀት ሁሉ እዚያ ነዉ ምርጥ ዩኒቨርሲቲ።
የሚሊኒየም የሦስት ትዉልድ ፈርጦች
እንዴት ነዉ የምንጨፍር ታግተዉ በአፋኞች።

ማነዉ የሚደሰት ማነዉ የሚጨፍር
ሚሊኒየም ብሎ ከወያኔ ጋር።

ኃይሉን ሊያሳየን ነዉ አርአያ ሊሆን
በፈቃዱ ወጥቶ የሰዋ እራሱን።
በጨቀየዉ መሬት በወጣቱ ደም
ማነዉ የሚጨፍር በሚሊኒየም።
አሁን ሊለዩ ነዉ የእፉኝት ልጆች
በበጎቹ መሀል ያሉ ተኩላዎች።

ማነዉ የሚደሰት ማነዉ የሚጨፍር
ሚሊኒየም ብሎ ከወያኔ ጋር።

ሙሉነህ አትበሉኝ ጎሎብኛል እኔ
አንዱአለም ተጋርዶ አይኑ በወያኔ።
የኔነህ የምለዉ ብሩክ ልጅ አዛኝ
ዝብጥያ ወርዶ በግፍ ሲሰቃይብኝ።
ሚሊኒየም ብሎ የሚል ደፋ ቀና
ታሪክ አይረሳዉም ከሀዲ ነዉና።

ማነዉ የሚደሰት ማነዉ የሚጨፍር
ሚሊኒየም ብሎ ከወያኔ ጋር።

ከቶ እንዴት ሊረሱ ዕልፍ ዐዕላፎች
ደብተራዉ ፀጋየ እነዚያ ምርጦች።
በትግራይ ወያኔ ታፍነዉ በጉድጓድ
ሚሊኒየም ብሎ እንዴት ነዉ ሽርጉድ።
አንድ ሆነን እንጩህ በያለንበት
ሚሊኒየም ይሁን ማብቂያ የእንግልት።

ማነዉ የሚደሰት ማነዉ የሚጨፍር
ሚሊኒየም ብሎ ከወያኔ ጋር።

ብርሀኑ እንዲበራ መና እንዲወርድልን
ቄሱ ዳዊት ይዞ ሁሌ የሚደግምልን፡፤
አንዳርጋቸዉ ብሎ ባህታዊ ዘግቶ
ዘወትር ሲፀልይ ለኢትዮጵያ ተግቶ።
እኛ ሚሊኒየም ልንመታ ዳንኪራ
ይለያል ዘንድሮ የሕዝብ ባላጋራ።

ማነዉ የሚደሰት ማነዉ የሚጨፍር
ሚሊኒየም ብሎ ከወያኔ ጋር።

በአስቻለዉ ከተማ ሞትና እርዛት
ጌታቸዉ ይፈርዳል ሆኖ ሰማይ ቤት።
አስራት የሚከፍሉት ልጆቹ በቅን
ቀርቧል ሊያሳያቸዉ ብርሀኑ መስፍን።
ከነፍስ ገዳዮች ይቅር ዛሬ ኅብረት
በደም ከታጠቡ የሚሊኒየም ዉጤት።

ማነዉ የሚደሰት ማነዉ የሚጨፍር
ሚሊኒየም ብሎ ከወያኔ ጋር።

ላለፉት ዘመናት ኖርን በጦርነት
በረሀብ በበሽታ በስደት ባርነት
ከእንግዲህ ይብቃን እስር ሞት እንግልት
ሚሊኒየም ይሁን ለሁላችን ህብረት።
ዛሬ እናሳያቸዉ ወያኔዎችን
ነፃ የምንወጣበት አንድነታችንን።

ማነዉ የሚደሰት ማነዉ የሚጨፍር
ሚሊኒየም ብሎ ከወያኔ ጋር።

ሚሊኒየም ይሁን ለእኛ መማማርያ
ለኢትዮጵያ ልጆች ይቅር መባባያ።
እፍረታችን ይብቃ ስደት ዉርደታችን
ከልመና እንዉጣ በሚሊኒየማችን።
እጃችን ይዘርጋ በአንድነት እንዘምር
ቃሉ ይፈፀም ዘንድ በቃል ኪዳን አገር
በእናት ኢትዮጵያ በያዕቆብ በኩሽ ምድር።

ማነዉ የሚደሰት ማነዉ የሚጨፍር
ሚሊኒየም ብሎ ከወያኔ ጋር።

ከአስጊ - ( በርን - ስዊዘርላንድ )
የካቲት 2 ቀን 1999 ዓ. ም.

 


 
`

@2007 - KINIJIT Support Organization In Switzerland Web Design By SaNet