Kinijitswiss.org contact us
Kinijitswiss.org Kinijitswiss.org Kinijitswiss.org
 


 
main content
?
ማን ነው የታስረው?
(አንዱ አለም - ከስዊዘርላንድ )
Audio (Mp3 ) (Real Audio)

ሁሌ ተደናግጦ - ሁሌ ተሸብሮ፣
በፀየፈ ተግባር - ሁሌ አቀርቅሮ፣
ሲወጡ ሰገቡ - ሁሌ ተደብቆ፣
ፍቅር ካላገኙ - ከሰው ጋር ተኑሮ፣
ስህተት ካላረሙ - ካለፉት ተምሮ፣
ሰው መባል ምንድነው?
.... የቱስ ላይ ነው ኑሮ!?

ሰው እውነትን ንቆ!?
.በሐሰት ተዘፍቆ፣
ከእሱነት መለያው ከሕሊናው ርቆ፣
ከጊዚያዊ ስጋው - ከንዋይ ተጣብቆ፣
ከነገ ክቡር ስም - የዛሬ ሆድ ልቆ፣
ደስታን ሳያሸቱ - ከሕዝብ ጋር ስቆ፣
ገላን ለይስሙላ - በከፈን ደብቆ፣
ሁልጊዜ ተጨንቆ - ሁልጊዜ ተሰቆ፣
እንኳን በሐገር ላይ - ባህር ማዶ ርቆ፣
አዳራሽ ለመግባት - ዙርያ ተጠብቆ፣
ሲገቡ በጓሮ - ሲወጡ በጓሮ፣
ኑሮ ነው አትበሉኝ - የቱ ላይ ነው ኑሮ!!
የቋጠሯትስ ብር - መቼ ቀን ተበልቶ፣
ምን ቀን ተረጋግቶ - ሁሌ እንቅልፍን አጥቶ፣
ታዲያ
ስው ራሱን አስሮ - ነፃነቱን አጥቶ፣
ሰውን እንዴት ያስራል - ምን አቅም አግኝቶ!?
ሽቦ አጥር ቢያጥሩ - ብረት ቢከምሩ፣
ፈራሽ ገላን እንጂ - እውነትን አያስሩ፣
ቢሮ ቢሰብሩ እንጂ - መንፈስን አይሰብሩ፣
ጉዞ የጀመረን የነፃነት እሳት ...
... ለአፍታ ቢገቱ እንጂ - ጨርሰው አይቀብሩ፣
እናም አስተማሩ፣
በሕዝብ ደም ሰርፀው - እነዚህ ሲኮሩ፣
ዓለም ሳቀባቸው - እነዚያ አፈሩ፣
.. እና መች ታሰሩ!?
እስቲ እንለየው - ማን ነው የታሰረው!?
እነዚያ ተበተን ተለያዩ ሲሉ፣
እነዚህ በፍቅር አንድ እንሁን አሉ፣
እነዚያ ጥላቻን ቂም ሲያቆጣጥሩ፣
እንዚህ ምህረትን ...
ይቅር መባባልን - ፍቅርን አስተማሩ፣
እነኚያ በሃይል - በጥይት ሲያመልኩ፣
እነዚህ በብዕር - ጥይት ይቅር አሉ፣
ሃገርህን ጥለህ - ተሰደድ ሲባሉ፣
ለጊዚያዊ ጥቅም - ለሆድ ሳያደሉ፣
ደስታውም ሐዘኑም ..
ከሕዝባችን ጋራ ባገራችን አሉ፣
እነኚያ ተጨንቀው - እንዲያው ሲያስመስሉ፣
ከሚድያ ጀርባ - አለን አለን ሲሉ፣
ያብሮነትን ክብር - እነዚህ አሳዩ፣
ሆ .! እያለላቸው - ምድር ሳር ቅጠሉ፣
ሕዝብ መሃል ገብተው ፍቅር ይህ ነው አሉ፣
እናም ሰርፀው ገቡ፣
በሕፃን በአዛውንቱ እየተሞገሱ፣
ስያሜ እስኪቸግር - መንፈስ እስኪባሉ፣
በጠለቀ ቅርበት - አካሌ ተባሉ፣
እናም በሕዝባችን በደሙ ውስጥ አሉ፣
ታድያ መች ታሰሩ? - ማን ነው የታሰረው?!
እነዚያ ተጨንቀው - እንዲህ ሲዳክሩ፣
ለሃሰት ውንጀላ - አለት ሲቆፍሩ፣
ምስክር በሆዱ - በእራፊ ሲቀጥሩ፣
በበጎ ሥራቸው - እነዚህ ግን ኮሩ፣
ካገራቸው አልፈው - ለዓለም በዋሉ፣
በዚህ ሰአት እንኳ - ሃገርን አስጠሩ፣
እነዚያ እንዳሉት - ሃገርም አልካዱ
.... ዘርም አላጠፉ፣
ይልቅ ዘር ያጠፋን - ሊዳኙ ሄዱ እንጂ
.. እውነትን ሊያጣሩ
ዓለም ይህን ሲያውቀው ፣
በገሃድ እያየው፣
እየመሰከረ እየሸለማቸው!
አሰርን ይላሉ - ጉድ እማይከብዳቸው!
... በርግጥ ቢጨንቃቸው ፣
መላ ቢጠፋ እንጂ - አይገፉት ገጥሟቸው፣
የሚሰሩት ስራ - ሀቁ መች ጠፋቸው፣
ተከሳሽ ተገርሞ - እየሳቀባቸው ፣
ጠበቃም አናቆም - ብሎ ሲንቃቸው፣
ችሎት ተደናግጦ - ተጨነቀባቸው::
እናስ ወገኖቼ - ማን ነው የታሰረው?!
መታሰር ምንድነው?!
በብረት መካለል - የዓመታት ፍዳው፣
አለመለመ እንጂ - ይበልጥ አጎመራው፣
የማንዴላን ትግል - ማን ጀግና ቀበረው!?
እና እስኪነቁ እንጂ .
.. ሰው መሆን ገብቷቸው፣
እነኚህ ሥራ ላይ ተልዕኮ ላይ ናቸው፣
ቀልጦ እሳት መሆንን - ሞቶ ሰው ማዳንን ፣
ታስሮ ማስፈታትን እያስተማሯቸው
ጀግኖቹስ ሥራ ላይ ተልዕኮ ላይ ናቸው፣





 
`

@2007 - KINIJIT Support Organization In Switzerland Web Design By SaNet