Kinijitswiss.org contact us
Kinijitswiss.org Kinijitswiss.org Kinijitswiss.org
 


 
main content

መጋቢት 23. 1999 ዓ.ም

ይድረስ ለሀገሬ ልጆች
ግልባጭ፡
ለሚ/ር ግሌን አንድሬስ
የአሜሪካን እርዳታ ድርጅት አ/አበባ

አንድ ግራ የሚያጋባ ከዚያም በላይ የሚያሳዝን ጉዳይ ገጠመኝና ዘወትር በህይወት ውጣ ውረድ ልቤን የሀዘን ቆፈን ሲመታው አንደማደርገው ወደ መጽሀፍ ቅዱሴ ሄድኩ። ለገጠመኝ ሁኔታ መልስ ፍለጋ ሳይሆን የመጽናናትና የነጻነት ሁሉ ጌታ የሆነውን የአምላካችንን መመሪያ በያዝኩት ጉዳይ ላይ ለመረዳት ነበር ወደምወደው አንድ የመጽሀፍ ክፍል የሄድኩት። መጽሀፈ ምሳሌ ላይ ይህንን እገኘሁና ልቤን የእውነት መንፈስ ሞቃት፤

" አባይ ሚዛን በአግዚአብሄር ፊት እስጸያፊ ነው
እውነተኛ ሚዛን ግን ደስ ያሰኘዋል"
መጽሀፈ ምሳሌ ( ምዕራፍ 11 ቁጥር 1 )

አዎን ሀዘን በቤታችን፣ በግል ህይወታችን፣ በመንደራችን፣ በምንወዳት ሀገራችንና በአለም ጉዳይ ሁሉ ባጋጠመን ጊዜ መብረር ያለብን ወደ እውነት አለቃ፣ ወደ እውነት መሰረትና ራሱ እውነት ወደ ሆነው እግዚአብሔር ብቻ ነው።

ዘወትር እንደማደርገው ይህንን መልዕክት በጻፍኩበት ቀን የሀገሬን ውሎ አዳር በተገኘው መጠን ለመረዳት በርከት ወደአሉት የመረጃ ድረ ገጾች እየገባሁ ፍሬ ነገሮችን ስቃርም ዐይኔ አፍቃሪ ህወሃት/ኢህአዴግ ወደሆነው የአይጋ ፎረም መሪ ዜና ላይ አረፈ። ዜናው አዲስ ፎርቹን በሚባለው ሀገር ቤት የሚታተም የአቶ በረከት ስምዖን ጋዜጣ የአሜሪካ እርዳታ ድርጅት ወይንም በእንግሊዝኛው United States Agency for International Development (USAID) ስራ መሪ የሆኑትን ግለሰብ በ1997 ቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ላይ የሰጡት አስተያየት ነው ለመጻፍ ከቸገረው እልልታ ጋር ያሰፈረው። የኢትዮጵያን ፓለቲካዊ ሁኔታ ጠንቅቆ ለሚረዳ የግለሰቡ አስተያየት እምብዛም ነገሬ የሚባል አይደለም። ዛሬ ሕዝባችን ስለዕለት ተዕለት ሕይወቱና ስለሀገሩ ወቅታዊ ሁኔታ የፈረንጅ ተንታኝና አስተንታኝ የሚፈልግበት ሁኔታ ላይ አይደለምና ያለው። በበኩሌ እኔን ያሳሰበኝ ለደቂቃዎችም ያስቆዘመኝ ፈጣሪያችን ለሰው ልጆች ነጻነት የገባውን ቃል ኪዳን ትተን ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ የገቡትን ቃል መከተል ስንጀምር የሆነው ሁሉ ነው።

በመጀመሪያ የአሜሪካ እርዳታ ድርጅት ስራ መሪው ያሉትን በቀጥታ የራሳቸውንና የእኔንም ግርድፍ ትርጉም ለሀገሬ ሰዎች ላጋራ፡

"That is a whole other set of political issues that I am not an expert in. I was not here in 2005 but I think we did have an observer group here during the election, including President Carter himself, and we felt that the opposition had lost the election. While there were a number of expressions of concern, and condemnation for the killings that occurred, we think some of our other donor partners had gone over board in encouraging the opposition and making them think that somehow they had won the election; we never believed that."

" . በ 1997 ቱ ምርጫ ወቅት እኔ እዚህ አልነበርኩም ቢሆንም ፕሬዝዳንት ካርተርን ጨምሮ የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን ስለነበረን ተቃዋሚዎች በምርጫው እንደተሸነፉ እናምናለን። ምንም እንዃ ብዙ አሳሳቢ ሁኔታዎች ምርጫውን ተክትሎ ቢከስቱም ፣ የተከሰቱትን ግድያዎች በተመለከተም ውግዘቶች የነበሩ ቢሆንም አንዳንድ የልማት እርዳታ አጋሮቻችን ብዙ ርቀት ሄደው ተቃዋሚዎችን ሲያበረታቱና ምርጫውን እንዳሸነፉ እንዲሰማቸው እንዳደረጉ ይስማናል ይህንንም አመለካካት በፍጹም አናምንበትም። "
እንግዲህ ያለማቛረጥ የ "ነጻነትና ዲሞክራሲ አፍቃሪዎቹን" አሜሪካውያን አጋርነት ፈልገን አንዴ አስር ሺዎች በተገኙባቸው ሰልፎች፣ አንዳንዴም ለወራት ባልተቋረጡ የሻማ ማብራት ፕሮግራሞች፣ ሌላ ጊዜም በአቤቱታ ደብዳቤዎች ወይንም ፒቲሽንስ ከዚህም ጎን ቀጣፊም ተበዳይም በኪሱ መጠን በሚታገልበት የደላላ ፖለቲካ በእነርሱ አነጋገር ሎቢንግና አድቮኬሲ ያደረግናቸው ሙከራዎች ሁሉ ይህንን መሰል መልስ ከፈረሱ አፍ አሰምተውናል።

የመልዕክቴን ተቀባይ ተጠቃሹ የእርዳታ ድርጅት ስራ መሪ ማድረግ እርሳቸውም "በሚያውቁት" ቋንቋም መጻፍ አልከበደኝም ነበር። ነገር ግን ከአሁን በኋላ በግሌ መጽሀፍ እንዳለው ዘወትር እየቀጠፉ ጸያፍ የሆነውን ነገር የሚያደርጉትን የምማጸንበት በቅጥፈት የደነደነ ልባቸውንም ደጅ የምጠናበት አጋጣሚ እንዳይኖር ለራሴ ቃል ገብቻለሁ። ይህ አንድም ፍትህን ከባቢሎን በመጠበቅ የፍትህን አምላክ መናቅ ይሆናል። ሁለትም ከትናንት አለመማር ነው።

ውድ ወገኖቼ !

የዕጣ ፈንታችን መሰረት የሆነችውን ሀገራችንን ዘወትር ወደምንናፍቀው የፍትህና የዲሞክራሲ መንገድ ጉዞ ትጀምር ዘንድ መሰረታዊውን ጉዳይ ከልባችን እንረዳ። ኢትዮጵያን በፈጣሪ እርዳታ ያለ ልጆችዋ በቀር ማንም ትንሳኤዋን እንደማያቀርብላት ከአንገት ሳይሆን ከአንጀት እንመን። ኤሎሄአችን እውነትንና መሰረቱን እንዳመቸ ከሚተረጉሙት ሀሰተኞች ዘንድ አይሁን። በዘመናት የሰው ልጆች ታሪክ ዕጣ ፈንታቸውን በገዢዎቻቸው ችሮታ ላይ ጥለው ነጻነትን ሀሴት ያደረጉ፣ ከምንጯም የተጎነጩና ካባዋን ደርበው የሞቁ የደመቁ ሕዝቦች ዐለም አልመዘገበችም። የቅርቡን የኢትዮጵያ ታሪክ ያስታወስን እንደሆን ይህንኑ ነው ከአባቶቻችን የምንማረው። የባሪያ ፈንጋይነት ወርተራው ለእኛስ ለምን ይቀራል ያሉት ጣልያናውያን በ18 ኛው ክ/ዘመን መጨረሻ ኢትዮጵያን ለመውረር እበሯ በከተሙ ጌዜ አፄ ሚኒሊክ የታላቋ ብሪታንያን ውግዘትና ተከትሎም እርዳታዋን እንደ መሪ ግባቸው አልወሰዱም። ለነጻነቱ ቀናኢ የሆነውን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ እምነቱ ለነጻነቱ ፈጣሪውን ተማፅኖ የጦር ዘንጉን ወልውሎ እንዲከት ነው ጥሪ ያደረጉለት። ይህንን ነው በማንም ዲስኩር ጥላሸት የማይቀባ ታሪክ ጥለው ያለፉት አባቶቻችን ያስተማሩን። በሐገር ላይ ችግር በተደቀነ ጊዜ ወደ ወንድም፣ ወደ እህት መመልክትን ! አባቶቻችን ባርነት እበራፍ በተደቀነ ጊዜ ለተማጽኖ ወደ ባዕዳን ቤተ መንግስት እንድንተም አላስተማሩንም።

ውድወገኖቼ !

በኢትዮጵያ ታሪክ ፊት ሞሶሎኒም፣ ግራዚያኒም ፣የቱርክና የግብጽ ፓሻዎችም ፣መሀዲዎችም ፣ኢሳያስ አፈወርቂም እንደሰይጣን በነው የሚጠፉ የሰይጣን ጃንደረባዎች ናቸው። ዛሬም በኢትዮጵያ ታሪክ ፊት ጆርጅ ቡሽም ፣ ኮንዶሊዛ ራይስም ፣ ዶናልድ ያማሞቶም ወዘተ ምንም አይነት ተገቢ ስፍራ አይኖራቸውም እኛ ባርነትና ኢፍትሃዊነት ሞቀውን ከክንብንባችን ለመገለጥ የእነርሱን እርዳታ የግድ ካላልን በቀር። የኢትዮጵያ ታሪክ የምንሰራው እኛው ልጆቿ ብቻ ልንሆን ይገባል። ሐገራችንን ወደ ፍትሕ ጎዳና ለመውሰድ የባዕዳንን የለበጣ ዲስኩር መጽሀፍ ቅዱሳችን አልያም ቅዱስ ቁርዐናችን አናድርገው። በንትርክ ብዛት ሊከስም ያለውን የነጻነትና የልበ ሙሉነት መንፈስ አለምልመን እኛው እጅ ለእጅ ተያይዘን እገደሉ ጫፍ የቆመውን የባርነትና የጎሰኝነት ተምሳሌት የሆነ አገዛዝ ወግድ እንበለው። እንዲህ ሲሆን ነው ዛሬ እየሰማነው ያለውን አይነት ሕወሃት/ ኢሕአዲግ ምርጫውን አሸንፏል አይነት የአርፋጅ ምስክሮች ሐተታ ለንፋስ የምንሰጠው።

የኢትዮጵያ ትንሳኤ ከአምላኳ ለጥቆ ነጻነት አፍቃሪ፣ ትሁትና ለመማር ዝግጁ በሆኑት ልጆቿ እጅ ላይ ነው። በቁርጥ ቀን አምላክ የሰጠንን የነጻነት ተምሳሌቶች መርሆዎች እናንግብ እንጂ የባዕዳንን ፈሊጥ አንቅዳ። ብርቱካን ሚደቅሳን አይነት የፍትህ ትንታግ ምሳሌ ማድረግ ትተን ኮንዶሊዛ ራይዝ ደጅ ሻማ በማብራት ጊዜ አናባክን። መስፍን ወልደ ማርያምን የመሰለ የመርህና የሰብዐዊነት ዋርካ እቃሊቲ ወርውረን እንደነፋስ ወፍጮ የሚሽከረከር መርህ ያለውን ዶናልድ ያማሞቶን አንለማመጥ። በዚህ ቀውጢ ወቅት የእውነት አምላክ በኢትዮጵያ ነጻነት ሊሰጥ የሚችለውን ሁሉ ችሯል። ለነጻነትና ለወገኖቻቸው ብሩህ ሕይወት ሲባል ሞትንም ቢሆን ግባ የሚሉ መሪዎች አሉን። ሕዝብን ለመረሸን አፈሙዛቸውን ከወለወሉ አልሞ ተኳሾች ፊት ለፍትህ ሲባል ዘብ የሚቆሙ ሚሊዮን ትንታግ አፍቃሪ ዲሞክራሲ ወጣቶች አሉን። ኢትዮጵያ በታሪዃ ለመጀመሪያ ጊዜ ለማለት ይቻላል ኢፍትሀዊውን የሕወሃት/ ኢሕአዲግ የፍርድ ቤት ዙፋን ለእውነት ሲሉ የፈነገጡ ዳኞችና ዐቃቤ ሕጋዊያን አግኝታለች። ከእውነት አንደበትነት ውጪ ከኤዲቶሪያል ቢሮ ምቹ ወንበሮች ይልቅ የሕወሃት/ ኢሕአዲግ ማሰቃያና ማጎሪያዎች ይሻላሉ ያሉ አንድና ሁለት ሳይሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ የሕዝብ ልሳን ጋዜጠኞች አሉን። ስንቱን በረከት ቆጥረን እንዘልቃለን እንጂ ለነጻነትና ፍትህ ሲባል ከሕወሃት/ ኢሕአዲግ ማዳበሪያ በረሀብ መሞትና በእስር መማቀቅን የመረጡስ አዕላፍ የነጻነት ታጋይ ገበሬዎችስ አሉንስ አይደል? ወገኖቼ ይህንን የነጻነት በረከት፣ ይህንን የነጻነት ሻማ ነው ከጋኑ አውጥተን እፍትህ ማማ ላይ ሰቅለን ለማንቦግቦግ ባዕዳንን ችላ ብለን እኛው መተባበርን ትግላችንን ፈር ማስያዝ የሚገባን።

መልዕክቴን ስደመድም ይህንን ደብዳቤ ለመጻፍ ለቆሰቆሱኝ የአሜሪካው የዕርዳታ ድርጅት የስራ መሪ የምለውን ልበል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ድርጅትዎና መንግስትዎ የተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎችና ረሀብ ለልመና ባስገደዱት ወቅት ለተደረገለት ልገሳ የምንግዜም ባለውለታዎች መሆናችሁን አይዘነጋም። ዛሬም ሕዝባችን የፍትህና የነጻነት ርሀብ ጠርንፎት ዐይኑ የፍትህ እያለ ያማትራል ፣ ከናፍሩም ነጻነትን ተጠምቶ ደርቋል፣ ልቡም የዲሞክራሲ ያለህ እያለ ይቃትታል። የመንግስትዎንና የመሪዎችዎን ቃል ሰምተን እመንግስትዎ መንበር ደጅ አቤት ማለታችንን ሳይሰሙ አይቀሩም። ዕሪታችን የፍትህ አጋር ቢያበጅልን የመንግስትዎን ጓደኝነት ቢተልምልን በወደድን። ያም ባይሆን ከወራት በፊት እንደነበረው መንግሰትዎ ገለል ብሎ እንዳላየ እንዳልሰማ ችላ ቢለንም ችላ የሚለው መመሪያዬ ያለውን የራሱን መርሆዎች ስለሆነ ቅር ብንሰኝም አምላክ ብቻ ስለሆነ ያለውን የሚያደርግ በድካማችሁ አናፌዝም። ነገር ግን እንደእርስዎ ያለ የመንግስትዎ ሎሌና መንግስትዎ በቁስላችን የጋለ ብረት ሲመስጉ ሕመሙን አንችለውም።

የነጻነት አምላክ ኢትዮጵያን ይባርክ !
ሳምሶን ብርሀኑ - ስዊትዘርላንድ




 
`

@2007 - KINIJIT Support Organization In Switzerland Web Design By SaNet