Kinijitswiss.org contact us
Kinijitswiss.org Kinijitswiss.org Kinijitswiss.org
 


 
main content

እየሰመጠ ያለ ዝናብ ግዱም አይደለም !

አንድ ቆየት ያለ የቻይናውን ተረት አለ። በአንድ የቻይናውን ግዛት የነበረ ንጉስ እጅግ ሲበዛ ሙዚቃ አፍቃሪ ስለነበር ወደ ሶስት መቶ የሚጠጉ ታዋቂ ሙዚቀኞች የሚገኙበት የሙዚቃ ቡድን እንዲመሰረት አድርጎ በየእለቱ የእነርሱን ጣዕመ ዜማ እየኮመኮመ ነፍሱን ያስደስት ነበር።

በዚሁ የሙዚቀኞች ቡድን ውስጥ ሚስተር ጉዎ የሚባል የሚጫወተውን የሙዚቃ መሳሪያም ይሁን የሙዚቃም ጥበቡ ያልነበረው አንድ አታላይ ሰው ነበር። ከሶስት መቶዎቹ ሙዚቀኞች መሀል የእርሱ ችሎታ በውል የሚለይበት አጋጣሚ ስላልነበር ከሙዚቀኞቹ ጋር " እየሞዘቀ" ማንም ሳያውቅበት የሀሰት ጠቢብ ሆኖ ለአመታት ይኖር ነበር።

ጊዜ ማለፉ አይቀርምና ንጉስም ያርፉና ልዑሉ ዙፋኑን ይወርሳል። ለሚስተር ጉዎ ችግር የሆነው የአዲሱ ንጉስ የሙዚቃ ፍቅር ከቀድሞው መለየት ነው። እኚህኛው የህብረት ሳይሆን የተናጠል ወይም ሶሎ የሚባለውን ሙዚቃ ይወዱ ስለነበር እያንዳንዱ ሙዚቀኛ በወር ተራ ሙዚቃውን እንዲያቀርብ ፕሮግራም ይወጣለታል ። በዚህም ምክንያት የሚ/ር ጎዎ አጭበርባሪነት ገሀድ ይወጣል የሀስቱም ካባ ተገፎ እርቃኑን ይቀራል።

በቅርቡ አቶ ልደቱ አያሌው ወደ መድረክ ብቅ ይሉና ሶስተኛ ስለሚባል መንገድ ሊሉ የሚችሉትን ሁሉ ይላሉ። ነገሩ እንደ ሚ/ር ጎዎ አይነት ጨዋታ መሆኑ ከታወቀ ስንብቶዋልና እጅግም ስለዚሁ መንገድ የተደነቀም መረር አድርጎ የያዘውም አልነበረም። ችግሩ ያለው የእኛዎቹ ሚ/ር ጎዎዎች አሁንስ ታውቆብኛል ማምታቱንም እዚሁ ይብቃ አለማለታቸው ላይ ነው። አንዱ ዘዴ ያሉት የማጨበርበሪያ ስልት ሲታወቅ ደግሞ ሌላ ነገር ይዘው ብቅ ይላሉ። እንዲያውም በቅርቡ ዋልታ የተባለው የህወሃት የፕሮፓጋንዳ መ/ቤት ያዘጋጀውን አቶ አየለ ጫሜሶና አቶ ተመስገን የሚባሉ ስዎች እኔ ነኝ ቅንጅት እያሉ የሚያደርጉትን መነታረክ ለተመለከተ ህዋሃት እንዴት ያለ ፌዝ የሚወድ ድርጅት እንደሆነ የበለጠ ይረዳል። በቅርቡ ደግሞ የዚሁ የህወሃት ስሪት የሆነ ሌላ ፊዝ በሌሎች ሰዎች ሲተወን ከርሞአል። የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን " ተቃዋሚ" ፓርቲዎችን የሆነ ትዕይንት ቤጤ እንዲሰሩለት ያስብና ኑና ተከራከሩ ሲል ጥሪ ያቀርባል። ነገሩ አዲስ በተሰኘው የምርጫ ህግ ላይ ነበር መሰለኝ። የተከበሩ ዶ/ር በየነ ጲጥሮስ የሚመሩት " ህብረት" የተስኘው ፓርቲ ኢዴአፓ/ መድህን በውይይቱ የሚገኝ ከሆነ አልሳተፍም ይልና ማዕቀብ ይጥላል። አንዳንድ ፓርቲ ትናንሹ ነገር ላይ ጠንከር ይላል እንጂ ዶ/ር በየነ " ፓርላማ" ከገቡና ታማኝ ተቃዋሚ ከሆኑ በሁዋላ የተዋናይ መረጣ ውስጥ ገብተው ከእገሌ ጋር አልተውንም ለምን እንዳሉ ግልጽም አልነበረም። ፓርላማ ውስጥ ከአቶ ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ከተወኑ ከአቶ ቡልቻም ጋር ይሁን ከክቡር አቶ ክህደቱ አፍያለው ጋርም ቢተውኑት ያውም ፈረንጆቹ ለወጥ ያለ ነገር /ቫራይቲ ስለሚወዱ አዲሱ የዲሞክራታይዚሽን ሂደት የሚባለው ተውኔት የተሻለ በመሰለ ነበር።

ነገሩን ከሌላ አቅጣጫ ለተመለከተው ደግሞ የዶ/ሩ አቛም ሚ/ር ጎዎ ተነቅቶብሃል ያነገትከውን የሙዚቃ መሳሪያ መጫወት አትችልም ስታብል ነው እያሉ ይመስላል። እስከዛሬ እውነተኛ ሀገር ወዳድ መስለህ ከህዝብ መሀል ገብተህ ስታምታታ የነበረው የግንቦቱ ምርጫ እርቃንህን አስቀርቶሀል ልክ እንደ ሚ/ር ጎዎ ሀዝብ በሶሎ/በተናጠል ማን ምን እንደሆነ አይቶዋል ለይቶዋል ያሉ ፤ቃሊቲ ያሉት መሪዎች የደረሰባቸው የመከዳት እጣ ፈንታ ዳግም በእርሳቸው እንዳይመጣ የፈሩም ይመስላሉ።

ነገሩ በዚህ አላበቃም። ሪፓርተር የተባለ የገዢው ፓርቲ ጋዜጣ ደግሞ ለምን የተከበሩ አቶ ክህደቱ ይነካሉ በሚል ይሁን በሌላ ምክንያት ዶ/ሩን " እርቃኖን አውቅዎታለሁ" ሲል በርዕሰ አንቀጽ ካርቱን አስደግፎ እንዳይሽጡ እንዳይለወጡ አድርጎ ይዘልፋቸዋል። ይሄው ሪፓርተር ዶ/ሩ ፓርላማ የገቡ ቀን በመላው አፍሪካ እርሳቸውን የመሰለ በሳል ፓለቲከኛ የለም ሲል አድንቆዋቸው ነበር። አሁን ዶ/ሩ የተሰመረላቸውን ቀይ መስመር ያለፉ ሲመስሉ ነው እንግዲህ ራቁትህን የማውቅህ አይነት ነገር የመጣው። የተከበሩ አቶ ክህደቱም ግልጽ ደብዳቤ ባሉት የዶ/ሩን አቛም ይተቻሉ።

ወደ ቁም ነገሩ ስንመለስ  ቧልተኞች እንዲህ ታላቅ ቁም ነገር ባለው የሀገር ጉዳይ ላይ ሲቀልዱ ይውላሉ። ባለሶስተኛ መንገደኞችንም፤ የፓርላማዊያኑን ህብረት ተብዪዎቹንም፤ ነጻ ጋዜጣ ነኝ ባዪን ፌዘኛውንም አንድ የምንላቸው ነገር ያለ ይመስላል። እንደ ሚ/ር ጎዎ ጌዜ ማ ምን እንደሆነ ለህዝብ ገልጦ አሳይቶዋል። ሁሉም በተናጠል ይምል ይገዘት የነበረውና ሆኖ የተገኘው  በግልጽ ታይትዋል። አህያ በአንድ ወቅት ነብርን በድምጹም በምኑም አስፈራርቶ ይሆናል ነገር ግን ይህንኑ ስልቱን በደጋገመው ቁጥር ራሱን ነው ያታለለው። የአህያ ማንነት እያደር ለነብር ግልጽ እየሆነ ሲሄድ የሞኝ ፈሊጡ ይበልጥ ወደ ሞት እያቀረበው ይሄዳልና። ለማንኛውም ሁሉም ወደ ልቦናው የሚመለስበትና ከሚር ጎዎና አልያም ክአህያይቱ ብልጠት የሚሰውረን ቀን እግዚያብሄር ያመጣ ዘንድ እንጸልይ።

ሳምሶን ብርሃኑ ( ስዊትዘርላንድ )




 
`

@2007 - KINIJIT Support Organization In Switzerland Web Design By SaNet